ሐሙስ 16 ኦክቶበር 2025

ንብ ተከትዬ ባይ ጎጃም ኖራ ማሬ

 ፍቅር እስከ መቃብር›_ ቴዎድሮስ ካሳሁን


ቴዎድሮስ ካሳሁን(Teddy Afro)
ፍቅር እስከ መቃብር
---------------------//--------------------
ግጥም - ቴዎድሮስ ካሳሁን
ዜማ - ቴዎድሮስ ካሳሁን
ሙዚቃ ቅንብር - አቤል ጳውሎስ /ናደው/
---------------------//--------------------

የፀበል ዳር እንኮይ ወንዝ ያወዛት ቅጠል፣
ተሸፍና ዋርካ ከልሏት የዛፍ ጥል፣
የት ነበር ያረግሁት ቀፎየን ስል ኖሬ፣
ንብ ተከትዬ ባይ ጎጃም ኖራ ማሬ።
ብራናዬ... አንች የልጅነቴ ጓዴ፣
ተረሣሽ ወይ የእሳት ዙሪያው ተረት ባንዴ፣ ብራናዬ... አንች የልጅነቴ ቀለም፣
እኔ እንዳንች ያጠናሁት ፊደል የለም። ፍቅር የበዛባት ሠማሁ ከማንኩሣ፣
መንናለች ቢሉኝ ቢጫ ልብሥ ለብሣ፣
ሸዋ ከሩፋኤል ስጠብቃት ኖሬ፣
ንቤ ገዳም ገብታ ጎጃም ኖራ ማሬ፣
ሲኖዳ ዮሃንስ ያመት ወዜን ይዤ፣
ጋማ ሽጦ ካሣ ሸኝቶኝ ከወንዜ፣
መጥቼ ከሸዋ ስጠብቃት ኖሬ፣
ለካ ገዳም ገብታ ጎጃም ኖራ ማሬ።(2)
ሀ ብለህ ተው ድገም ሲሉኝ ንሥሃ አባቴ፣
ዋ ብዬ ተማርሁኝ ወይ አለመስማቴ፣
ቀለም ወርቄ ቢሆን የቅርቤ ጓደኛ፣
ፍቅር ለያዘው ሠው ከልካይ የለው ዳኛ።
አሁን በማን ስቄ የልቤን ልካሠው፣
አንዴ በእሷ ፍቅር የተረታሁኝ ሠው፣
የት ርቄስ ባገኝ ከፍቅሯ መሸሻ፣
እሷ ሆና ለኔ ያለም መጨረሻ።
ማር ጧፍ ሆኜ...
ማር ጧፍ ሆና....
ማሬ ማሬ...
ጎጃም ጉራማይሌ፣
ማሬ ማሬ...
ጎጃም ጉራማይሌ፣
ኦሆሆሆ....
ማር ጧፍ ሆኖ... ገባ መቅደሥ፣
ነዶ ለኔ... ፀሎት ሊያደርሥ፣
ዲማ ጊዮርጊስ... ላይ ማንኩሣ፣
ያቺ ወንጌል... ቢጫ ለብሣ፣
ከንግዲማ... ቆብ አስጥዬ፣
እንዳልወስዳት... አባብዬ፣
ሠብልዬ ናት... እማሆዬ፣
ሠብልዬ ናት... እማሆዬ፣
ሠብላለም...
በቢጫው ቀለም፣
ሠብለኣዳም...
ገባሽ ወይ ገዳም፣
ወይ ገዳም....
ገባሽ ወይ ገዳም...
የፀበል ዳር እንኮይ ወንዝ ያወዛት ቅጠል፣ ተሸፍና ዋርካ ከልሏት የዛፍ ጥል፣
የት ነበር ያረግሁት ቀፎየን ስል ኖሬ፣
ንብ ተከትዬ ባይ ጎጃም ኖራ ማሬ። አ...አሃሃይ...
አ...አሃሃይ...
ብራናዬ... አንች የልጅነቴ ጓዴ፣
ተርሣሽ ወይ የእሣት ዙሪያው ተረት ባንዴ፣ ብራናዬ... አንች የልጅነቴ ቀለም፣
እኔ እንዳንች ያጠናሁት ፊደል የለም። ላሳደገኝ ደብር የሥለት ልጅ ሆኜ፣
ካህን እንዴት ይፍታኝ ያንቺ እሥረኛ ሆኜ፣ በጊዜ ተደፋ የቀለሙ ቀንዴ፣
የኔ ፊደል መሆን ካንቺ አዳነኝ እንዴ። ሣዋህድ ከኖርሁት ቅኔን ከደብተሬ፣
ተሽሎኝ ተገኜ ባላንዲሩ ገብሬ።
ለካ ሠው አይድንም በደገመው መጽሓፍ፣ እንደሠም አቅልጦ ፍቅር ካረገው ጧፍ፣
ለካ ሠው አይድንም በኦሪቱ ገድል፣
ወንጌል ይዞ መጥቶ ፍቅር ካረገ ድል።
ማር ሲገባ ገዳም ድንጋይ ተንተርሶ፣
ጧፉም እንደመናኝ ህይወት ቢጫ ለብሶ፣ ወንጌል መነኮሱ በልጅነታቸው፣
ማር እስከጧፍ ሆኖ ዓለም ቢነዳቸው።
አንች የፍቅር ጥጌ ውድ ነሽ በጣሙን፣ መምጣቴ ነው በቃ እኔ አቃተኝ አሁን፣
አዲስ ዓለም ሆነ ባንቺ ሥል ወጋየሁ፣
እድሌ ሆነና ባጣሽ ተሠቃየሁ።
ማር ጧፍ ሆኜ...
ማር ጧፍ ሆና...
ማሬ ማሬ...
ጎጃም ጉራማይሌ፣
ማሬ ማሬ...
ጎጃም ጉራማይሌ፣
ኦሆሆ......
ማር ጧፍ ሆኖ... ገባ መቅደሥ፣
ነዶ ለኔ... ፀሎት ሊያደርሥ፣
ዲማ ጊዮርጊስ... ላይ ማንኩሣ፣
ያቺ ወንጌል... ቢጫ ለብሣ፣
ከንግዲማ... ቆብ አስጥዬ፣
እንዳልወስዳት... አባብዬ፣
ሠብልዬ ናት... እማሆዬ፣
ሠብልዬ ናት... እማሆዬ፣
ሠብላለም...
በቢጫው ቀለም፣
ሠብለኣዳም...
ገባሽ ወይ ገዳም፣
ወይ ገዳም....
ገባሽ ወይ ገዳም...
ዘንግ ይዛ.....

የቴዲ ጎፈር ‹‹ሰብለ አለም››

 ደረጀ ኅብስቱ derejehibistu

ቴዎድሮስ ካሳሁን ርዕሱ ‹ኢትዮጵያ› በሚለው አልበም ፥ ያልተዳሰሱ ያልተነሱ የኢትዮጵያ ጉዳዮች አሉ ለማለት ያዳግታል። ‹‹ንብ ተከትዬ ባይ ጎጃም ኖራ ማሬ›› የምትለዋ የፍቅር እስከ መቃብር ትረካው ግን፥ ለእኔ ጎጃም እስከ መቃብር ሆናብኛለችና፥ ቴዲ አፍሮን በጎጃምኛ ስሙ፥ ቴዲ ጎፈር ብዬ ሰይሜ ጎጃም ላስመንነው ነው፡፡ በጎጃም አካባቢ፥ ፀጉሩን የሚያሳድግ ሁሉ ‹ፀጉሩን አጎፍሯል› ይባላልና፥ ቴዲ ጎፈር እንበለው። መልካም ምናኔ፡፡

‹‹ማሬ ማሬ
ጎጃም ኖራ ማሬ›› እንዴታ! ጎጃምማ ማር ናት፡፡ ማር በንቧ ብዙ ድካምና ልፋት እንዲገኝ፤ ጎጃምም በልፋት በድካም ትገለፃለችና፡፡ የጎጃም ማሯ ትምህርቷና ጤፏ ናቸው፤ በብዙ ድካምና ውጣ ውረድ ገንዘብ ያደርጓቸዋል እንጂ በዋዛ አይቀመሱምና፡፡ ጎጃም ትምህርቷን ልቅሰም ቢሉ፥ ከውሻ ተናክሰው፣ አኮፋዳ ይዘው፣ ደበሎ ለብስውና እከክ ወርሰው፥ በጭንቅ፣ በመከራ ይማሩታል እንጂ፤ አይስ ክሬም እየላሱ፣ ጌም እየተጫወቱ፣ ባክ ባግ ቦርሳ አንግተው አይደለምና፡፡ ጤፍም በአይን ሲያይዋት ትናንሽ ናት እንጅ፥ ትንሽ አንጀትን የምታልብ ድካም ያለባት ሰብል ናት፡፡ መሬቱን ሁለት ሦስቴ ደጋግመው አርስው፣ አለስልሰው፤ ዘር ዘርተው፣ በከብረት አስደቅድቀው፤ ጉልጓሎ ጎልጉለው፣ አረም ሁለት ሦስቴ ታርሞ በብዙ ድካም አድጋ፣ አፍርታ፣ ታጭዳ፣ ተወቅታ ጎተራ ትገባለች እንጅ፤ እንደ ቡና እሸት እየለቀሙ ጎተራ አይከቷትም። ጎጃምማ ማር ናት የምትላስ ወለላ፡፡
ንጉስ ካሌብ ከንግስናው በፍቃዱ ወርዶ ቢመንን የገባው ጎጃም ጣና ገዳም ነበር፡፡ ቅዱስ ያሬድ ሰነፍ ተማሪ እየተባለ በተወለደበት አካባቢ ቢወቀስ ጎጃም ገብቶ የዜማ ሊቅ ሆነ፡፡ ቅዱስ ላሊበላ የገዛ ወንድሞቹ እስከ እየሩሳሌም ቢያሳድዱት ጎጃም ገብቶ፣ በተማረው ጥበብ ሁሉንም አስከነዳቸውና የቅድስና ማዕረግን ተቀዳጅቶ ለዘመናት ምስክር የሚሆኑ ትክል ውቅር ህንፃ ቤተ ክርስቲያኖችን ቆርቁሮልን አልፏል፡፡ የአስራ ስድስተኛው ዘመን ፈላስፋችን ዘርዐ ያዕቆብ እንኳ በተከሰተው ችግር ተማርሮ ሊሰደድ የወደደው ወደ ጎጃም ነበር፤ ምንም እንኳ እንፍራነዝ የሌላ ሃገር መስሎት እንፍራን ሃብቱ ቤት ተጠለልኩ ቢለንም፡፡ ጎጃም ረቂቅ ቅኔ ናት!
‹‹የጸበል ዳር እንኮይ፤ ወንዝ ያወዛት ቅጠል›› የወንዝ ዳር እፀዋት ከልምላሜ፣ ከአበባ፣ ከፍሬ አይለዩም፤ አመት እስከ አመት ከሐመልማል አይታቀቡም፡፡ ሰብለ አለም በቤተሰቦቿ ቤት እንደ ጸበል ዳር እንኮይ፣ እንደ ወንዝ ዳር ቅጠል የፈካች ያማረች ጉብል ነበረች፡፡ ለቤተሰቦቿና ለአካባቢዋ ውበት የምትፈነጥቅ ስጋ ለበስ ሐመልማል፡፡
‹‹ብራናዬ አንቺ የልጅነቴ ቀለም፤
እኔ እንዳንቺ ያጠናሁት የለም››
በእርሷም ልጅነት በባልንጀሮቿም ልጅነት ውስጥ ከህሊና የማትለይ ማራኪ ቀለም፡፡ በልጅነት ዓይናችን ስንመለከት ሁሉም የልጅ ነገር ይሆናልና፤ በልጅነት ትውስታችን ዛሬም ጎጃም ልጅ ናት፡፡ ቀለሟ በህሊናችን ቀልሞ አልጠፋ ያለን የልጅነት መስፈሪያ መለኪያ፣ አለምን መመልከቻ መነጽር ያበጀንባት ብራናችን ጎጃም፡፡ እንደ ማንኩሳው ልጅ በዛብህ፡፡
‹‹ብራናዬ አንቺ የልጅነት ጓዴ
ተረሳሽ ወይ የሳት ዙሪያው ባንዴ››
‹‹ፍቅር የበዛባት ፈልቃ ከማንኩሳ፤
መንናለች ቢሉኝ ብጫ ልብስ ለብሳ››
ማሬ፣ ማሬ ሲላት፤ እንኮይ ሲላት፤ የልጅነት ቀለሜ፣ ጓዴ ሲላት የነበረችውን አሁን በመጠቅለያ ስሟ ‹‹ፍቅር የበዛባት›› ብሎ አመጣት፡፡ ሲማስንላት፣ ሲንገላታላት፣ ሲንከራተትላት የሚኖራት ጎጃሙን ፍቅሬ፣ ፍቅሬ እያለ ሊያሽኮረምማት ይከጅላል። ፍቅር በባህሪው መናኝ ነው፤ ሌላ ጠባይ አይስማማውም፤ ብቻውን ፍቅር ነው፡፡ ቴዲ ጎፈርም መንናለች ቢሉኝ ብጫ ልብስ ለብሳ›› ይላታል ፍቅሩን፤ መናኝ መሆኗን እንደ መርዶ ሁሉ ከሌሎች ነው የሚሰማው፤ ‹‹መንናለች ቢሉኝ›› ይለናልና። መናንያን ብጫ ልብስ ለብሰው፣ ያውም ወይባ ተጎናጽፈው ብርሃናዊ፣ መናኝ፣ ሰማያዊ መሆናቸውን ያሳያሉ፡፡ የቴዲ ፍቅሩ ወደ ጎጃም ያስመነነችው ብጫ/ወይባ አስለብሳ ነው፡፡ ሰብልዬ፣ ሰብልዬ እያለ ሲያንቆለጳጵሳት፤ ጎጃም ሰባተኛው ሰማይ ላይ ሰቀለችው፡፡ ‹‹ባሳደገኝ ደብር የስለት ልጅ ሆኜ፤ ካህን እንዴት ይፍታኝ ያንቺ እስረኛ ሆኜ›› እያለ በምድር የፈታችሁት በሰማይ የተፈታ ይሁን የተባሉት ካህናት እንኳን የማላገኝበት ያንቺ ፍቅር የሰባተኛው ሰማይ መናኝ አድርጎኛል የሚለን ይመስላል፤ ቴዲ ጎፈር፡፡ ‹‹ሸዋ ተሩፋኤል›› ይልና በዘዴ አማላጁን ሩፋኤልን ይጠራል፤ ሩፋኤል ፈታሄ ማህጸን ነውና፡፡ ሴቶች በወሊድ ጊዜ ምጥ ሲበዛባቸው ማህጸናቸውን ፈትቶ በሰላም እንዲገላገሉ ያደርጋል፡፡ ቴዲ ጎፈር የጎጃም ፍቅር ጠንቶበት በጭንቅ ሰባተኛው ሰማይ ላይ ሰቅሎታልና፤ ፈታሄ ማህጸን ሩፋኤል የሰማያትን ማህጸን እንዲፈታለት ይማጸነዋል፡፡
‹‹በጊዜ ተደፋ የቀለሙ ቀንዴ፤
የኔ ፊደል ማወቅ ካንቺ አዳነኝ እንዴ››
በድቁና ዘመኑ የጎጃም መኳንንትንና መሳፍንትን አፍ ያስከፈተው ጉብሉ በዛብህ፤ ባልታሰበ አጋጣሚ ፊደል እንዲያስተምራት በተሰጠችው ሰብለ የምትባል ምትሃታዊ ልጃገረድ አቅሉን ስቶ ጨርቁን ጥሎ አበደ፡፡ ‹‹ድጓ መማር መና፤ ማወቅስ ውሃ ዋና›› እንዳለው፣ የውሃ ሙላት ሚስቱን ሲወስድበት ታዛቢ እንደሆነው ደብተራ፤ የበዛብህ ቅኔ ማወቅ ከሰብለ ፍቅር ሊያስጥለው አልቻለም፡፡
‹‹ማሬ ማሬ ጎጃም ኖራ ማሬ›› እንዴታ! ጎጃምማ ማር ናት፡፡ በኦሪት ዘፍጥረት፣ በሙሴ ቃል ኢትዮጵያን የሚከበው ወንዝ የጎጃሙ ግዮን እንደሆነ ተጠቅሷል አይደል፡፡ ይሄው ግዮንም አይደል እንዴ ገነት ከሚያጠጡ አራት አፍላጋት አንዱ ነው የተባለ። ታዲያ ቴዲ ጎፈር፤ ጎጃምን ፍለጋ መንኖ ሰባተኛው ሰማይ አልወጣም የሚል አለ‘ንዴ? ይሄው በራሱ አንደበት እንዲህ ይለናል፡-
‹‹ማር ሲገባ ገዳም ድንጋይ ተንተርሶ፤
እዩት ጧፍ ገዳም ገባ ቢጫ ልብሱን ለብሶ››
ማር ባህሪ የተባለ ጎጃም ድንጋይ ትራሱ፣ ቅጠል ጉርሱ፣ ዳዋ ልብሱ ሆኖ ገዳም ሲገባ ቢያየው፤ እንዲሁም ማር ባህሪ የሆነች ሰብለ ወንጌል ፀብዐ አጋንንትን፣ ግርማ ሌሊትን ተቋቁማ ድንጋይ ተንተርሳ፣ ጤዛ ልሳ፣ ዳዋ ጥሳ ገዳም ገባች፤ የፍቅር ጧፍ የምሆን ቴዲ፤ ከማር ተለይቼ ጧፍ መሆን፣መኖር፣ መብራት መስጠት፣ ብርሃን መፈንጠቅ አይቻለኝምና ጎጃም መንኛለሁ ይለናል። ጧፉ ቴዲ ጎፈር፤ ወይባ ለብሼ ተከተልኩ እያለም አይደል እንዴ፡፡ ምስጢር ለማመስጠር ስፍራ አልበቃው ብሎ እየፏለለ ጎጃም ይገባል፤ ጧፉ ቴዲ፡፡
‹‹ማር ጧፉኔ፣
ማር ጧፉና፤
ማሬ ማሬ፣
ጎጃም ኖራ ማሬ››
‹‹ማር ጧፍ ሆኖ ገባ መቅደስ፤ ነዶ ሌሊት ጸሎት ሊያደርስ›› ማር የተባለው ፍቅር ማርኮኝ፤ ጧፍ የሆንኩት እኔ ቴዲ ተያይዘን መቅደስ ገባን፤ በፍቅር እሳታችን ሌሊት በተባለው ጥላቻ ላይ እንደ ጧፍ ነድደን የምህረትና የቸርነት ጸሎት ከሚደርስበት ሰባተኛው ሰማይ ገነት ገብተን ምልጃ እያቀረብን ነው የሚለን ይመስላል፤ የጎጃሙ መናኝ ቴዲ ጎፈር።
‹‹ሰብልዬ ሰብልዬ ሰብለ አለም ኧረ ቢጫው ቀለም፤ ሰብለ አለም ገባሽ ወይ ገዳም›› በጭንቅ፣ በምጥ፣ በጋር የተያዘ ሰው ህመሙን ቢደጋግም ቢደጋግም ቢጠራው የሚሻለው የሚድን ይመስለዋልና፤ ስሟን ጠርቶ አይጠግበውም፤ ሰብለ ጎጃሙን፡፡ አልያዝ አልጨበጥ ብትለው ‹‹ኧረ ገባሽ ወይ ገዳም›› ይላታል፡፡
‹‹ማሬ ማሬ ጎጃም ኖራ ማሬ›› እንዴታ! ጎጃምማ ማር ናት፡፡ ጎጃሜ ጉብል ልጁን ሲወዳት ሰብለ ይላታል፡፡ መሬት አርሶ፣ ዘር ዘርቶ፣ አረም አርሞ እንደሚንከባከባት ሰብል ሁሉ ‹‹ሰብለ›› ይላታል የሚወዳት ልጁን፡፡ የሃዲስ አለማየሁ የ‹‹ፍቅር እስከ መቃብሯ›› ሰብለ እንዲህ ያለች ሰብል ናት (ሰመሬታ ሰብስቤ የምትባለውን የዩኒቨርሲቲ ጓደኛቸንን በምን እናስታውሳት ታዲያ በዚህ ካልሆነ)፡፡ የተደከመባት፣ የተንከራተቱላት፣ የሚመንኑላት፣ የመነነች ሰብል። ጎጃም ሲመንኑላት ትመንናለች፤ ስትመንን ይመንኑላታል፡፡ በምናኔ በብቸኝነት ተሰልቃ፣ ተደቁሳ፣ የምትጠፈጠፍ እንጎቻ ናት ጎጃም፡፡ ጎጃምን ይበሏታል እንጂ እሳቷን አይጋሯትም፡፡ ‹‹ማሬ ማሬ ጎጃም ኖራ ማሬ›› እንዴታ! ጎጃምማ ማር ናት፡፡ ጎጃም ሽናሻ፣ አገው፣ ሻንቅላ፣ ዴንሳ፣ ስናን፣ ቀራንዮ፣ ጉንድ፣ ጮቄ፣ ሶማ፣ ባሶ፣ ጃዊ፣ ቻግኒ፣ ወንበራ፣ መተከል፣ ወይጦ፣ ደንቀዝ፣ እንፍራንዝም ናት። ‹‹ሳዋህድ ከኖርኩት ቅኔ ከደብተሬ፤ ተሸሎ ተገኜ ባላንዲሩ ገብሬ›› ጎጃም የባለዋሽንት ባላገር፣ የቅኔ፣ የቀለም ውህድ ሃገር መሆኗን ለማሳየት የኛው ቴዲ ጎፈር ስሪት፣ ንጥረ ነገራችንን እያወዳደረ፣ እያነጻጸረ ያሳየናል፡፡ ‹‹ለካ ሰው አይድንም በዖሪቱ ገድል፤ ወንጌል ይዞ መጥቶ ፍቅር ካደረገ ድል›› ይለናል፤ እርሱን ብቻ ሳይሆን ጎጃም፣ ፍቅር፣ ሰብለወንጌል ሁሉንም አሸንፋለችና።
‹‹አንቺ የፍቅር ጥጌ ወርቅነሽ በጣሙ፣
መምጣቴ ነው በቃ እኔ አቃተኝ አሁን፤
ሃዲስ አለም ሆነ ባንቺ ስል ወጋየሁ…›› ይላል ቴዲ፡፡
ሃዲስ ዓለም የማየት ወግ የሚያደርሰን የጨለማውን መገለጥ የንጋቱን ውጋግ የሚያሳየን መሲህ ከጎጃም ያገኘ እየመሰለው፡፡ የቴዲ የፍቅር ጌጡ ጎጃም ወርቅ ከነጣዕሙ የሚያጣጥምባት መሆኗን ያውቃልና፤ ቀድሞ ገና ቀጠሮ ያስይዛታል - ‹‹መምጣቴ ነው በቃ እኔ አቃተኝ አሁን›› እያለ፡፡ የመሲህ መምጫው በጭንቅ በመከራ ነውና፤ ጭንቅ መከራ የሚበዛባትን የጎጃም ማር ለመላስ፣ ከመሲኋ ጋር ቃል ለቃል ለመመላለስ የሚናፍቅ የሚሽቀዳደም ይመስላል፡፡ ‹‹የት ነበር ያረኩት ቀፎዬን ስል ኖሬ፤ ንብ ተከትዬ ባይ ጎጃም ኖራ ማሬ›› የክርስቶስን መወለድ በኮከብ ምልክትነት አውቀው ኮከቡ መንገድ እየመራቸው ቤተልሔም በግርግም ለተወለደው ህጻን እንደ ሰገዱ ሰብዐ ሰገሎች (ጎጃሜውን ዘርዐ ደሽትን ጨምሮ) ቴዲም ንብ ተከትሎ፣ ጎጃም ገብቶ የናፈቀውን መሢህ ያገኘ ይመስላል፡፡
ዊንተር ፓላስ የሚባል የሩሲያ አረቄ ያለ መለኪያ እየተቀዳልኝ፤ ከመነንኩበት ሃሳብ ስነቃ፣ ክለብ ዩጎቪያ ውስጥ መሆኔን ተረዳሁ፡፡ ጋባዥ ጓደኞቼ ከእነመኖሬም እረስተውኝ ዳንኪራቸውን እያስነኩት ነው፡፡ የሚዘፈነውም ዘፈን የጃኖ ባንዶች እንደ ሚዳቋ እየተዘለለ የሚናጡበት ነው። ምንድን ነው እዚህ ሃሳብ ውስጥ የከተተኝ፡፡ ምናልባት ቀን በተደጋጋሚ የቴዲ አፍሮ አዲሱ አልበምን ስንሰማ ስለቆየን ይሆናል፡፡ ጩጬው ጓደኛዬ ፊቱ በሙሉ ላብ በላብ ሆኖ እስክስታውን ይለዋል። ፊቱን ፀሐይ አስመስሎ ሌላኛው ጓደኛዬ ዝላዩን ያጦፋል። እንዳሻው የሚምነሸነሸው ሌላው ጓዴ ወለሉ ጠቦታል፡፡ እኔ በእኩለ ሌሊት መሲህ ከጎጃም እጠብቃለሁ፡፡
‹‹ሃዲስ አለም ሆነ ባንቺ ስል ወጋየሁ፤
 የእድሌ ሆነና ባንቺ ተሰቃየሁ
ማር ጧፉኔ፣
ማር ጧፉና፤
ማሬ ማሬ፣
ጎጃም ኖራ ማሬ››


‹‹የገርማሞ ልጅ ተገርሞ ሊያስገርመን?››
(( ደመቀ ከበደ - ማንኩሳ - ጎጃም ))
የፀበል ዳር እንኮይ ወንዝ ያወዛት ቅጠል
ተሸፍና ዋርካ ከልሏት የዛፍ ጠል….
የት ነበር ያረኩት ቀፎየን ስል ኖሬ
ንብ ተከትዬ ባይ ጎጃም ኖራ ማሬ
ፍካሬና እማሬ ለግጥም ሁነኛ ተቀብኦዎች ናቸው ይላል ፕሮፌሰር ተሾመ ይመር (የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲው የቋንቋ መምህር)፤ ሀሳብህን ስትፈክረው እማሬውን (ኑባሬውን) አታሳጣው መሆኑ ነው፡፡ ቴዲ ፈክሯልም፤ አዕምሯልም፡፡ እንኳን መሃል ሸገር ላደገው እሱ ቀርቶ ከእኔ ጋር ጥጃ ለጠበቀ የጎጃም (በጥቅሉ የክፍለ ሀገር) ሳተናም እንኳይ የሚበላ የዱር ፍሬ መሆኑን ከዘነጋነውና የአማርኛ ቃል ስለመሆኑም የሚጠራጠር አይጠፋም፡፡
‹‹እንኮይ እንኮይ እንኮይ
የኔ ፉርኖ ዳቦ ልግመጥሽ ወይ››
የሚል ቆየት ያለ ተወዳጅ ዜማ በኢትዮጵያ ሬዲዮ አዳምጥ ነበር፡፡ በልጅነቴ ምንም የገጠር ከተማ (ሞጣ ቀራኒዮ ባድግም) የትምህርት መዘጋትን ተከትሎ ሰኔ ግም ሲል፣ ሀምሌ ከነደመናው አገሩን ሲወረው ከወንዝ ሙላት ታግለን እንጨት (ጭራሮ ለቀማ) ገጠር ወደ ጫካ ስንሰማራ ትዝ ይለኛል፡፡ በተለይ ሶታነት ሲሰማን በነበረ ጊዜ (በከተምቾው በፈነዳን ጊዜ) የብብታችንን ፀጉር፣ የጉልበታችንን ስር ጭገርና የፂማችንንና ሸንጎበታችንን (የከንፈር የላይኛው ፀጉር) የበለጠ ለማጥቆርና ‹ደርሰናል› ለማለት በምላጭ ለመፈግፈግ እንዲመቸን እንጨት ለቀማ መሄድ የምንናፍቀው ጉዳይ ነበር፡፡
በሁለት ምክንያት የበለጠ እወደው ነበር፤
አንድ - ማንም ሳያይ የጉርምስና ውጤቶቼን ለማየት (የአካላቴን ለውጥ)፣
ሁለት - የዱር ፍሬዎችን ለመብላት፡፡ ሾላ፣ ዶቅማ፣ ዋንዛ፣ እሼ፣ …. እና እንኮይ!!
እንኮይ ቢጫ ቀለም ያለው፣ የቄብ ዶሮ እንቁላል የምታክል ኮምጠጥ የምትል ግን ኮምጣጤነቷ ጣፋጭነቷን የማያግድባት እንደሎሚ ያልጠነከረ ገላ ያላት፣ ልስላሴዋ እንቁላል የሚመስል ግን ፍፁም ክብ የሆነች ፍሬ ነች፡፡
እንኮይ በገጠሩ ዘመዶቼና ለእንደኔ አይነቱ ገጠሬነት ናፋቂ ለጎረምሳው የፍቅር ስጦታ፣ ለጎልማሳው የሶታነቱ ትዝታ ናት፡፡
በእንጨት (ጭራሮ) ለቀማ ጊዜ ጎረምሳና ኮረዳ አንድ ላይ ቢሄዱ ነውር የለበትም፤ አንድ ላይ ቢለቅሙም እንደዚያው፡፡ የተፈቀደ የፍቅር መጀማመሪያ ሁነት ነው የሚመስለን፡፡ ከየዛፉ ቆርጠን፣ በአኮፋዳችንና በየኪሳችን ጠርቀን ካጠራቀምን በኋላ ለየከጀልናት ደበቅ እያረግን እንሰጣለን፡፡ በጄ ካለችና ልቧ ከከጀለ ትቀበላለች፤ ካልሆነም አትቀበልም፡፡
እንኮይ ግን እንደዶቅማ ቶሎ አይገኝም፡፡ በእርግጥ ከአካባቢ አካባቢ ካልተለያየ በቀር እኛ ዘንድ ውድ ነበር፡፡ ውድነቱን እንወደው ነበር፤ ለፍተን ደክመን ስናገኘው ለወደድናት የምንሰጠው ውድ ነገር ነበርና፡፡
አሁን የገርማሞ ልጅ
‹‹የፀበል ዳር እንኮይ ወንዝ ያወዛት ቅጠል
ተሸፍና ዋርካ ከልሏት የዛፍ ጠል›› በሚለው ስንኙ
‹‹የፀበል ዳር እንኮይ…›› ሲል በፍቅር እስከ መቃብር ውስጥ በዛብህ ለሰብለወንጌል ፍቅር ውዴታውን ከእንኮይ ጋር ማዛመዱ በፍካሬም በእማሬም ሰምሮለታል፤
‹‹ወንዝ ያወዛት ቅጠል›› ሲላት ደግሞ ያች የፊታውራሪን ወተትና ቅቤ እየጠጣች ያደገች ኮረዳ ትምቡኬ ገላዋና ጉንጯ በዓይነ ህሊናችን እንድትመጣ ‹‹ምስለ ክሰታውን›› ሰማይ አድርሶታል፤
በዚያም ላይ ዓባይ ጎጃምን እንደመቀነት ዞሯታልና ወዲያውም በገጠር ቀዬዎች ዓባይ ዓባይነቱን (ላልቶ) ብቻ ሳይሆን ፀበልነቱን የሚቀበሉትም ባላገሮች አሉና ባህላዊ እሴቱን (ፎክሎሩን) አጢኖታል ያስብለዋል፤
‹‹ተሸፍና ዋርካ…›› ብሎም ያሳምረዋል፡፡ በፊውዳሉ የነፊታውራሪ ዘመን ‹‹ክብር›› እንደ መርግ ለሚጫናቸው መሸሻ ሰብለ ከእልፍኝ የማትወጣ ብትሆን ቁብ አይባልም፡፡ በዛብህ መሸሻና መሸሻነታቸው ከዋርካ ቢገዝፈው፣ ዘመኑ ከመርግ ቢከብደው፣ ፍቅር ባፈዳው ኮስማና ገላውና ጢቢኛ ልቡ የሚቻለው አይደለም፤ እንደዋርካ ትልቅ ዛፍ የለም፡፡ እንደ ዋርካ ረጅም ዕድሜ የሚቆይም እንዲያው፡፡ በዚያ ላይ የጊዜው ባለጊዜ ነበሩ ፊታውራሪ፡፡
‹‹ተሸፍና ዋርካ…›› ይለንና ‹‹ከልሏት የዛፍ ጠል›› ን ሲደግመው ይህ ድጋሜ ልቀቱን ያረቀዋል፡፡ ትልቁ ዋርካ በስሩ ያሉትን ዛፎች ሁሉ ደቃቃ ያደርጋቸዋል፡፡ ዋርካ ግንዱ ብቻ ሳይሆን ቅርጫፉም ሰፊ ነው፡፡ ስለዚህ እንኳን በዝናብ ጊዜ በፀሀይ ወቅትም ጥላው ይቀዘቅዛል፤ ሲዘንብ ከየቅጠሎቹ የሚረግፈው ጠፈጠፍ (ጠል) እንደጤዛ ቶሎ አይረግፍም፤ ጥላውም ጠሉም ቀስ ያለ ነው የዋርካ፡፡ ስለሆነም የዋርካ ስር ተክሎች ሁሉ ቢያድጉም አይጎመሩም፡፡
ሰብለም ለበዛብህ እንዲያ ማለት ናት፡፡ የዋርካው ጠል የስሩን ተክሎች እንደማያስጎነቁላቸው፣ ቢያጎነቁሉም እንደማያስጎመራቸው ሁሉ ሰብለም የ‹‹ዋርካው ቤተሰቧ›› ጠል ተጭኗት ያልጎመራች ነበረች፡፡ የዋርካው ስር ተክሎች ወዲያ በቅርጫፉ፣ ወዲህ በግንዱና በስሩ እንደተቀፈደዱት ሁሉ ሰብለም በፊታውራሪ የታሰረች ‹‹የለመለመች ግን ያልጎመራች ቅጠል›› ነበረች፡፡
የገርማሞ ልጅ ‹‹ፍቅር እስከ መቃብር››ን ሞዝቆታል፤ ተቀኝቶታል፣ ፈክሮታል፣ አዕምሮታልም፡፡ በፈረንጅኛው extratextual art ሰርቶ ነጥሮበታል። ከጥበብ ስራ ላይ ሌላ ጥበብ አውጥቷል።
‹‹የት ነበር ያረኩት ቀፎየን ስል ኖሬ
ንብ ተከትዬ ባይ ጎጃም ኖራ ማሬ››
ይህ ስንኝ ደግሞ እንድምታው ሸጋ ነው፡፡
ቀፎ እንዳዛሬው ዘምኖ ደጅ ሳይሰጣ፣ በጭራሮና በቀርቀሃ ሳጠራ እየተሰራ ዛፍ ላይ ነበር የሚሰቀል፡፡ ጎጃም የቀይ ማር አዘማሪ፣ አምራችና ጠጃም ነው፡፡ ጠላ እንኳን ተጠምቆ ውብ ሲሆን ‹‹ጠጅ ያስንቃል›› ነው እሚል፡፡
ለጎጃሜ ጤፍ እንጀራው እህሉ ሲሆን ማር ወጡ ነው፤ የዛሬን አያድርገውና፡፡
ባላገር በሞላ በጋውን ያሽሞነሞነውን ቀፎ የበልጉን መብለግለግ፤ የክረምቱን መስገምገም ያይና ከዛፎቹ መሀል ይሰቅለዋል፤ አንዱን ሳይሆን እልፉን፡፡ የቀፎው ብዛት የዛፉን ቅርንጫፍ ያህል ቢሆን ነው፤ ዋርካ፣ ግራር፣ ዝግባና ብሳና የመሰላሰሉ ቅርንጫፈ ብዙ ዛፎች ከሆኑ ባላገር ታድሏል፤ ብዙ ቀፎ ይሰቅላል፡፡
አደይ አበባይቱን ዘፍኖላት፣ መስከረሚቱን አዚሞላት ጥቅምቲቱ ደረስኩ ስትለው ያገሬ ባላገር ‹‹የጥቅምት ማር›› ቆረጣ ይጀምራል፡፡ እየፎከረ እንደሚያጭደው ማኛ ጤፉ እየዘፈነ ጭስ እያጠነ ማሩን ይቆርጣል፡፡
ብዛቱ ‹‹ቀፎዬ የት ነው›› ሊያስብለው ይችላልና በሰበቡ ጎረቤቱ ጋር ሊጣላና በክትክታና ወይራ ሽመል ሊናከት ይችላል፡፡
ማር ለጎጃሜ ጥፍጥናው፣ ውዴታውን መግለጫው ነው፡፡ የወደደውን ‹‹ማር፣ ማርዬ፣ ማርዋ›› ይላል፡፡ ጥር ላይ ልጁን እንኳን ሲድር ‹‹ማሬ›› ብሎ ካልዘፈነ ይነሆልላል፡፡ የእምቦቃቅላ ልጁን የከንፈር ጠብታ (ለሀጭ) እንኳን ‹ማር› ጠብ ይለዋል ነው እሚል፡፡
ወዲህ በምስራቁ ጎጃም በደጀን፣ እነማይ፣ ደብረወርቅ፣ ደብረማርቆስ፣ ጎዛምን፣ ሁለት እጁ እነሴ (ሞጣ ቀራኒዮ) እና መርጡ ለማሪያም እስከ ባሶሊበን ባለው ቀዬ ‹‹ማሬ›› ብሎ ዘፍኖ ባሶ ምት መምታት (እስክስታ መውረድ) የባህሉ አንዱ አካል ነው፡፡
ወዲያም በምዕራቡ አዴት፣ ባህርዳር፣ ቡሬ፣ ፍኖተሰላም፣ ጅጋም አልባሶ መደንከር ወግ ነው ፤ ሁሉም ግን ማሬ ቢል ማር ከቀፎው ቆርጦ ነው፡፡
ማሪቱ ሰብለወንጌልም ከቀፎዋ ወጥታ የት ሄደች ብሎ በዛብህ ዓባይን ተሻግሮ ሲፈልጋት ልቡን ይዛ እዚያው ነበረች - ጎጃም፡፡
በጎጃሜ ንግግር ‹‹የት ኑረህ ነው?›› ካለህ ስፈልግህ ቆየህ፣ የትነበርክ እያለህ ነው ማለት ነው፡፡
ጎጃም ሲናገር ‹‹እዚህ ኑራ!!›› ካለ ‹‹ለካ እዚህ ነበረችና›› እያለ ነው ማለት ነው፤
እናም የገርማሞ ልጅ
….የት ነበር ያረኩት ቀፎየን ስል ኖሬ
ንብ ተከትዬ ባይ ጎጃም ኖራ ማሬ….
ሰብለ የትነች ስል በከበቧት ጀሌዎች ‹‹ንቦች›› የት እንዳለች አወኩ እያለህ ነው፡፡
‹‹ሰብለ ውዴ ጎጃም ነበረች ለካ›› ማለቱ ነው፤ እንጂማ ‹‹ማሬ ማሬ››ን ትዝ ሊያሰኝህም አይደል፤ እረ እሱ እቴ ጎጃሜ ኖሯል - ሸገር መስሎ!!
ለማንቻውም ወረታው ውበትም፣ ቻላቸው አሸናፊም ‹‹ማሬ፣ ማርዘነቤ፣ ማርዋ›› ሲሉ እሷን (ፍቅረኛቸውን) እየፈከሩ ማሩን እያዕመሩ ነው፡፡
ቀፎው የገርማሞ ልጅ ልብ በማሪቱ ሰብለ ሲነሆልል ንቦቹ ከበዋት እነፊታውራሪ ስር ነበረች፡፡
ኧሯ!!! ጎጃም ኖራ ማሩ!!!
ይህንን ጉድማ አሁን አናበቃውም፡፡
እያረፍን እያንዳንዱን ስንኝ እንዘልቃለን፣ በገባን ልክ እንሰልቀዋለን!
ወይ መታደልህ እያልን


ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ደብረ ገነት ነብዩ ኤልያስ ቤተ ክርስቲያን

  የሊቃውንት መፍለቂያ! ደብረ ገነት ነብዩ ኤልያስ ቤተ ክርስቲያን በምሥራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ኤልያስ ወረዳ የሚገኘው ደብረ ገነት ነብዩ ኤልያስ ቤተ ክርስቲያን በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአጼ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥ...